በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ22ኛ ጊዜ፣ በሀገራችን ለ21ኛ ጊዜ በመከበር ላይ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን በዩኒቨርሲቲያችን“ ትውልድን በስነምግባር ተቋምን በአሰራር “ በሚል መሪ ቃል በድምቀት ተከብሮ ውሏል ፡፡
በመድረኩ ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ገ/ምክኤል ወ/ገብርኤል እንደገለፁት ከመሪ ቃሉ በውል እንደምንረዳው በመልካም ስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ በየትኛውም የስራ እርከን ላይ ቢመደብ አገልግሎቱን በንጹህ ህሊና፣ በመልካም ስብዕና፣ በቅንነትና በታማኝነት ተደራሽ በማድረግ አገልጋይ ሆኖ እንደሚሰራና ለሀገር እድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ዘርፈ ብዙ መሆኑን መሪ ቃሉ እንደሚያመላክት ገልጸዋል ፡፡
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሙስና የፀዱና ከብልሹ ኣሰራር የራቁ እንዲሆኑ የተቋማቱ ኣሰራር በማዘመን፣ ሁሉም የኣሰራር ስርዓቶች ዲጂታላይዝ የማደረግ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባል ስሉ ፕረዚዳንቱ በኣፅንኦት ተናግረዋል።
ዶክተር ገ/ምክኤል ከዚህም በተጨማሪ ሁላችንም በየተሰማራንበት የስራ መስክ በመልካም ስነምግባር የታነጸ ፣ተገልጋይ ተኮር የሆኑ አገልግሎቶችን በመስጠት ዩኒቨርሲቲው የራሴ ነው በሚል እሳቤ “ ትውልድን በስነምግባር ተቋምን በአሰራር “ የሚለውን መሪ ቃል ከንድፈ-ሃሳብ ባሻገር በተግባር የዕለት ከዕለት የሰራ ዲሲፕሊናችን በማድረግ ፣ተማሪዎችም የመጡበትን ዓላማ ለአፍታም ሳይዘነጉ የዕውቀት አባት/እናት የሆኑትን መምህራኖቻቸውን እንዲሁም በቆይታቸው በተለያየ መልኩ በመልካም ስነምግባር ለሚያንጻቸው የግቢው እና የአካባቢው ማህበረሰብ እውቅና በመስጠት በመልካም ዓርአያነት የሚጠቀስ ዜጋ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ፕሬዝዳንቱ የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ፡፡
በመድረኩ ላይ ለተሳታፊዎች ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ከፌዴራል የተላከ በድምፅ የተዘጋጀ መልእክት ከመቅረቡም ባሻገር በምስራቃዊ ዞን የፀረ ሙስናና ስነምግባር ሓላፊ በኣቶ ምስጉን አማካይነት የመወያያ ጽሁፍ ቀርቦ ሰፊ የሆነ ውይይት ተካሂዶበታል።
በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንቶች የሀብት ምዝገባ በማካሄድ ከዩኒቨርስቲው ፀረ ሙስናና ስነምግባር ሓላፊ ኣቶ ሃፍታይ የርክክብ ስነስርዓት ኣካሂደዋል።
በመድረኩ የምስራቃዊ ዞን ም/ኣስተዳዳሪ ኣቶ ሃይላይ ጨምሮ ከዞኑ፣ ዓዲግራትና ጋንታ ኣፈሹም ወረዳዎች ከፍትሕ ተቋማትና ሌሎች የሚመለከታቸው ኣካላት ተገኝተዋል።