በዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሴቶችና ማሕበረሰብ ጉዳዮች ኣካትቶ ትግበራ ስራ አስፈፃሚ ኣዘጋጅነት “ጥቃትን የማይታገስ ማሕበረሰብ ለትውልድ ግንባታ” በሚል መሪ ቃል በአለም ለ34ኛ ግዜ በኢ/ያ ደግሞ ለ20ኛ ግዜ የነጭ ሪቫን ቀን የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር፣ የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች፣ ተማሪዎች እንዲሁም የዓዲግራት ከተማ የማሕበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት ተከብሯል ።
በመክፈቻ ስነ ስርዓት የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የሴቶችና ማ/ሰብ ጉዳዮች ኣካትቶ ትግበራ ስራ ኣስፈፃሚ ወ/ሮ ይርጋለም ነጋሽ በሴቶችና ህፃናት የሚደርሱ ማንኛውም ዓይነት ፆታዊ ጥቃትን ዝም ኣልልም የሚል ማሕበረሰብ እንዲፈጠርና ከማንኛውም ዓይነት የሴቶች ጥቃት ነፃ የሆነ ምቹ የስራ ቦታ ለመፍጠር ሁሉም በትብብር እንዲሰራ መልእክታቸውን ኣስተላልፈዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ፕረዚዳንት ተወካይ ዶ/ር ሃፍታይ ገ/የሱስ ነጭ ሪቫን ማለት በተለያዩ የስራ ቦታዎች ስነ ምግባር የጎደላቸው ወንዶች በሴቶች ላይ የሚፈፅሙት ፆታዊ ፣ ስነ ልቦናዊ፣ ወሲባዊ ትንኮሳና ማስፈራራትን መከላከል ነው ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ የሴች ጥቃት ለመከላከልና ለማስቀረት ሁሉም እጅ ለእጅ በመያያዝ በግንባር ቀዳምነት ሚናው ሊወጣ ይገባል ሲሉ መልእክት አስተላልፏል ።
በመድረኩ የፀረ ፆታዊ ጥቃት(ነጭ ሪቫን ቀን) የሚል መወያያ ፅሑፍ በሕግ መምህርት ስእለይ ሽበሺ ቀርበዋል። በቀረበው መወያያ ፅሑፍ በተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየት የቀረበ ሲሆን ፤ በአዘጋጆች ማብራሪያ እና መልስ ተሰጥቷል ።
የዩኒቨርስቲው ኣርት ክለብ ኣባላትም በመድረኩ ከዕለቱ ፕሮግራም ተያያዥ ያላቸው የስነ-ጥበብ ስራዎች ኣቅርበዋል።